Home Uncategorized ህዝብ ግምባሩን ለጥይት ሰጥቶ ነው ያስፈታን

ህዝብ ግምባሩን ለጥይት ሰጥቶ ነው ያስፈታን

SHARE

‹‹በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህግና ደንቡን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የጭቆና ስርዓቱን ለማስቀጠል የመፈለግ ነገር ነው የሚታየው››
‹‹ህዝብ ግምባሩን ለጥይት ሰጥቶ ነው ያስፈታን››
እስክንድር ነጋ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከስድስት ዓመት ተኩል የእስር ቆይታ በኋላ በይቅርታ ቦርድ ጥያቄ መሰረት መፈታቱ ይታወሳል፡፡ አቶ እስክንድር በእስር ቆይታው ወቅታ ስለነበረው ሁኔታና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኤፍሬም ተፈራ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ማያ፡- የእስር ቆይታህን እንደመነሻ እናድርገው? የእስር ጥሩ ባይኖረውም ምን ጠንካራና መጥፎ ጎኖች ነበሩት?
አቶ እስክንድር፡- ሁለቱም ነበሩ፡፡ ጠንክሬያለሁም፤ ተፈትኛለሁም ጠነከርኩ የምለው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው መንፈሳዊ ጥንካሬ ነው፡፡ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት የማንበብ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ አዲስ ኪዳንን በደንብ አንብቤያለሁ፡፡

ኦሪትንም በጥልቀት ለማንበብ እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን መፅሀፍ ቅዱስ እንዳይገባልኝ ስለተከለከልኩ ያንን ዕድል ልጠቀምበት አልቻልኩም፡፡ በእስር ዘመን ቆይታዬ ከሚያሳዝነኝ ነገር ሁሉ አንዱ መፅሐፍ ቅዱስን መከልከሌ ነው፡፡ ምንም ባደርግ መፅሐፍ ቅዱስ ልከለከል አይገባም ብዬ አምናለሁ፡፡

ማያ፡- መፅሐፍ ቅዱስ እንዳይገባ የተከለከለው ለምንድነው? አልጠየክም?

አቶ እስክንድር፡- እስር ቤት እያለሁ እፅፍ ነበር፤ እነርሱ የመጻፍ መብትህም ተገድቧል ይሉኛል፡፡ በዚህ መካከል አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ አትፃፍ ሲሉኝ እኔ ደግሞ መብት አለኝ ፍርድ ቤትም ሆነ እናንተ ልትከለክሉኝ አትችሉም እል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የተለዩ እስረኞች ወዳሉበት ቦታ ተወሰድኩ፡፡ እንደሚታወቀው በእስር ቤት ውስጥ ሌላ እስር ቤት አለ፡፡ ስለዚህ እኔም ወደዛ ተወሰድኩ፡፡ በሂደትም ወረቀት፤ እስኪሪብቶና የሚነበቡ ነገሮችንም ተከለከልኩ ማለት ነው፡፡
ማያ፡- ወደቀደመው ምላሽህ ተመለስልኝ፤ በእስር ሳለህ ስለነበረው ጠንካራና መጥፎ ጎኖች እያወራኸኝ ነበር፤

አቶ እስክንድር፡- ሁለተኛው ስለ ዲሞክራሲ ያለኝ እምነት እንዲጠናከር አድርጎታል (በነበረኝ የ6 ዓመት ከግማሽ ቆይታዬ) እኔ የታሰርኩት የግንቦት 7 አባል ነህ በሚል ነው፡፡ እኔ የግንቦት ሰባት አባል አልነበርኩም፡፡ እንኳን በእውኔ በህልሜም የግንቦት ሰባት አባል አልነበርኩም፡፡ እና ምን ያህል አንድ ህዝብ (በእኔ ላይ የደረሰ በደል በማንም ላይ ሊደርስ ይችላልና) በሰላም ለመኖር የህግ ዋስትና እንደሚያስፈልገው በተግባር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ዋስትና ስለሌለን፣ በአምባገነኖች እጅ ስላለን፤ እነሱ ከህግ በላይ ስለሆኑና ማንንም እንደፈለጉ ሊያስሩ ስለሚችሉ፤ ማንም ሰው የእኔ እጣ እንደሚያጋጥመውና ሀገራችንም ዴሞክራሲ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልጋት የተረዳሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ለዴሞክራሲ የነበረኝ እምነት ተጠናክሯል፡፡

ሌላው የፈተና ጉዳይ ነው፡፡ አዎ! በደንብ ተፈትኛለሁ፡፡ ከባለቤቴ ተለያይቻለሁ፤ ከልጄ ተለያይቻለሁ፤ ባለቤቴ ልጃችንን ይዛ ለመሰደድ ተገዳለች፡፡ ልጄ ደግሞ የተወለደው እስር ቤት ነው፡፡ በመከራ የተወለደ ልጅ ነው፤ አስራ አንድ ዓመት አብሮት የኖረ ነው፡፡ በትግል ውስጥ ተወልዶ በትግል ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ እረፍት አላገኘንም በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰላማዊ ታጋይ እስር እንደሚገጥመው ይታወቃል ስደትም፣ ሞትም ይገጥመዋል፡፡ ይኼንን መቋቋም የሚያስችል ስነልቦናዊ ዝግጅት ነበረኝ፡፡

ማያ፡- በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እፈታለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?

አቶ እስክንድር፡- በአጭር ጊዜ ውስጥ እፈታለሁ ብዬ አልጠበኩም፤ በተለይ በ2010 እንወጣለን የሚል ግምት አልነበረንም፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን ማታ እስር ቤት ውስጥ በር የሚዘጋው በ11 ሰዓት ነው፡፡ በአስራ አንድ ሰዓት በር ተዘግቶ በ12 ሰዓቱ ዜና ላይ (እከሌና እከሌን) ጨምሮ ከ400 በላይ እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ ተወስኗል የሚል ዜና ሰማን፡፡ በጣም ነው የደነገጥነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ይቅርታ ጠይቀን ይቅርታችን ይቅርታ ቦርድ ጋር የቀርበበት ነገር የለም፡፡ ዜናውን ስንሰማ ግር ብሎናል፡፡ በሌላም በኩል ደስ ብሎናል፡፡ ‹መንግስት እስረኞችን ለመፍታት ወስኖ ነው ማለት ነው?› አልን፡፡

በመነጋታው ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ቢሮ ተጠራሁና ፎርም አውጥተው ‹‹ይኸው መንግስት እናንተን ለመልቀቅ ወስኗል፤ ሆኖም ግን ለይቅርታ ቦርድ የሚሞላ ፎርም አለ ሙሉ›› ተባልን፡፡ ለጊዜው በጣም ነው ግር ያለን፤ በአንድ በኩል የይቅርታ ቦርድ እንዲለቀቁ ወስኗል ተብሎ ዜና ተነግሮ፤ በሌላ በኩል ገና ለይቅርታ ቦርድ የሚቀርብ ፎርም ሙሉ አሉን፡፡ በጣም ደነቀን፤ ለማንኛውም አንፈርምም አልናቸው፡፡

በነገራችን ላይ መንግስት አጣባቂኝ ውስጥ ገብቷል ብለን አይደለም አንፈርምም ያልነው፡፡ ቀደም ብሎ ገና ወደ ክሱ ሂደት ስንገባ፤ ሳይፈረድብን ይቅርታ አንፈርምም፤ ጉዳዩ በይቅርታ አይቋጭም ብለን ወስነን ነበር፡፡ አንፈርምም ስንላቸው ያንን ታሳቢ አድርገን ነው እንጂ፣ ከአንድ ቀን በፊት ‹‹እንዲፈቱ በይቅርታ ቦርዱ ተወስኗል›› ተብሎ ስለተላለፈ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ብለን አልነበረም፡፡ ይኼንን ለነርሱም በደንብ አስረድተናቸዋል፡፡ በዚህ ተለያየን፡፡

በዚህ ሁኔታ እያለን ሀሳባችን ሀምሳ ሀምሳ ከመቶ ሆነ፡፡ እምቢ ስላልን አይፈቱንም፡፡ አይ በሚዲያ ተናግረዋል ስለዚህ ይፈቱናል የሚል ውዥንብር ውስጥ ገባን፡፡ ኢህአዴግን እንደምናውቀው በአንድ ነገር ላይ አቋም ከያዘና አልስማማም ካልከው አይለቅህም፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል አንፈታም የሚል ነገር ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ በዚህ የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ እያለን ከተወሰነ ቀን በኋላ እንደገና ሚዲያዎች ‹‹እስክንድር ነጋንና አንዷለም አራጌን ጨምሮ አራት መቶ ምናምን እስረኞች ዛሬ ሊለቀቁ ነው›› የሚል ዜና ማስተላለፋቸውን ጓደኞቼ ነገሩኝ፡፡ አላመንኩም፡፡ ቀልድ ነው የመሰለኝ፡፡ እስፖርት ላይ ነበርኩ፡፡ ጨርሼ ሻወር ቤት እንደገባሁ እንደገና ቢሮ ተጠራሁ፡፡

እንግዲህ አልፈርምም ብላችኋል ግን የይቅርታ ቦርዱ እንድትፈቱ ወስኗል፡፡ ነገር ግን አንድ ፎርም አለች፤ ይህች ፎርም ከይቅርታ ጋር የምትገናኝ አይደለችም ማንኛውም እስረኛ ከእስር ሲፈታ የሚሞላው ነው፤ የማረሚያ ቤቱ ፎርም ነው አሉን፤ እኛም ‹‹ይቅርታ አሁንም አንፈርምም›› አልን፡፡ የማንፈርምበትንም ምክንያት አስረዳናቸው ማናቸውንም ፊርማ ብንፈርም ጭቅጭቅ የሚያስነሳ ቀዳዳ መክፈት ነው የሚሆነው ይኼን ጉዳይ የሚከታተል ህዝብ አለ፡፡ ለዚህ ህዝብ ደግሞ ቃላችንን መጠበቅ ስላለብን ነው አልናቸው፤ አልተከራከሩንም፡፡

በአስር ሰዓት ላይ እንደገና ተጠርተን ዕቃችሁን ይዛችሁ ውጡ ተባልን፡፡ ዕቃችንን ይዘን ስንወጣ በር ላይ ተፈትሸን ስንጨርስ ወረቀት አምጥተው ‹‹የይቅርታ ቦርድ ሰርተፍኬት ነው ውሰዱ›› አሉን፡፡ በይቅርታ እንደተፈታችሁ የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ነው፤ ይኼንን መውሰዳችሁን የሚያረጋግጥ ፊርማ ኮፒው ላይ ፈርሙ ተባልን፤ አሁንም አንፈርምም አልናቸው፤ ለህግ የበላይነት ተገዥ መሆን አለመፈለጋችን አለመሆኑን ደግመን ነገርናቸው፡፡ በአሁን ሰዓት በምንም ነገር ላይ ከፈረምን ፈርመዋል፤ አልፈረሙም የሚሉ ጭቅጭቆች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ትለቀቃላችሁ ከተባልን በኋላ እንኳን እነዚህን ሶስት ደረጃዎች አልፈናል፡፡

በአጠቃላይ መፈታታችን ተአምር ነበር፡፡ በእርግጥ ህዝብ ዋጋ ከፍሎበታል፤ ህዝብ ግምባሩን ለጥይት ሰጥቶ ነው ያስፈታን፤ ሞቶ ነው ያስፈታን፡፡ በኢህአዴግ ፍላጎት አይደለም የወጣነው ህዝቡ ምን ትፈልጋለክ ሲባል ‹‹የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ›› ብሎ ነው ያስለቀቀን፡፡ ለእግዚአብሄርና ለህዝብ ያለኝን አክብሮት እገልጻለሁ፡፡ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፡፡

ማያ፡- መንግስት እስረኞችን ለመፍታት በወሰነው ውሳኔ የተሰማህ ስሜት ምንድነው?

አቶ እስክንድር፡- ኢትዮጵያ በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይኼን የለውጥ እንቅስቃሴ በሁለት መንገድ ልትገልጸው ትችላለህ፡፡ መነሻው ግን ህዝብ ነው፡፡

ለሀያ ሰባት ዓመታት የዘለቀው የዴሞክራሲ ጥያቄ ውሎ አድሮ ተንከባሎ አሁን በስሏል፡፡ አሁን ህዝቡ የለውጥን ጥያቄ የህልውና ጥያቄ አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረው ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ በኢህአዴግ ውስጥም ተቀጣጥሏል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም የተወሰኑ የለውጥ ፈላጊዎች ብቅ ብለዋል፡፡ በስልጣን ሽግሽጉ ላይም የምናየው ነገር ይኼንን ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በገዥው ፓርቲ ውስጥም ሆነ በህዝቡም የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደገባች አመላክቷል፡፡

በየትኛውም ሀገር ብትሄድ አንድ ሀገር በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ስትገባ፤ አንድ አምባገነን መሪ ወደ ለውጥ ውስጥ ሲገባ ዋነኛው መገለጫ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ነው፡፡ በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገሮችም የታየ ነው፡፡ ስለዚህ የኛ መፈታት የለውጥ ጥሪ ነው፤ የለውጥ ደውል ነው፤ ጊዜው የለውጥ ነው የሚል ጥሪ እያስተጋባ ነው፡፡ ለዚህ የለውጥ ደውል ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ህዝቡም፤ ተቃዋሚዎችም ሁሉ ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲሆን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ የአንበሳው ድርሻ ግን የገዢው ፓርቲ ነው፡፡ አብዛኛውን ድርሻ ከሞራልም፤ ከታሪክም፤ ከፖለቲካም አኳያ ኃላፊነቱ በኢህአዴግ መሪዎች ትከሻ ላይ ነው፡፡

ማያ፡- አሁን ላለንበት ወይም ለደረስንበት ችግር ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ እስክንድር፡- ምክንያቱ የዴሞክራሲ አለመኖር ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለው ተሀድሶ ፍለጋ አይደለም፡፡ ለዚህ ሁሉ አለመረጋጋት ምንጩ ኢህአዴግ ለአስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ባለመስጠቱ ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱ ከዛ የበለጠ ጥልቀት አለው፤ ያ ምንድነው ህዝቡ ዴሞክራሲ ይፈልጋል፡፡

የሚፈልገው ዴሞክራሲ እንዴት ያለ ነው ሲባል ፍላጎቱን የሚገልፅባቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው የአንድ ህዝብ ፍላጎት የሚገለጸው በፖለቲካ ድርጅቶች በኩል ነው፡፡

ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ፍላጎቱን በህውሓት በኩል ይገልፃል፤ የትግራይ ህዝብ አንዱ መገለጫው ህውሓት ነው፤ አረና ነው፤ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ ያ ህዝብ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡን በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በኩል ይገልፃል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎቶች በተለያዩ ድርጅቶች ይገለጻል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ፡፡ ሌላው ደግሞ ህገወጥ የተባሉ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህም በዛ ህብረተሰብ ውስጥ ያለ ፍላጎት መገለጫዎች ናቸው፡፡

ህገወጥ የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው አስተሳሰቦች መገለጫ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ወደ ህጋዊ መድረክ መምጣት አለመቻላቸው፤ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ነው የችግሩ ምንጭ፡፡

ወደ መፍትሄው ስንመጣ፤ ይኼ አሁን ያለው የፖለቲካ ምህዳር ሰፍቶ፤ በህጋዊ መንገድ ብቻ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ህገወጥ የተባሉትንም ማቀፍ አለበት፡፡ ምክንያቱም በህዝቡ ውስጥ ያለን አስተሳሰብና ፍላጎት ስለሚወክሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ወደ ህጋዊ መንገድ የሚመጡበትን ነገር ማመቻቸት ነው መፍትሄው፡፡

ከደቡብ አፍሪካ ያየነው ተሞክሮ ይሄ ነው፡፡ ኢ ኤን ሲ ወደ ህጋዊ መድረክ ሲመጣ (ሌሎችም አሸባሪ ተብለው የነበሩት ወደ ህጋዊ መድረክ እስኪመጡ ድረስ ደቡብ አፍሪካ መረጋጋት አልቻለችም ነበር፡፡ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ኢ ኤን ሲ ወደ ህጋዊ መድረክ ሲመጣ (ሌሎችም አሸባሪ ተብለው የነበሩት ወደ መድረኩ ሲመጡ) ደቡብ አፍሪካ የዓለም የዴሞክራሲ ሞዴል ተባለች፡፡ አሁንም ነች፡፡ እኛም ጋር እንደዛ ነው መሆን ያለበት፡፡ ህገወጥ የተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ወደህጋዊ መንገድ የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን የምለው እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እያለ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ችግር ከስር መሰረቱ፤ ከምንጩ ለማድረቅ፤ ዘላቂ መፍትሔና ዴሞክራሲ ለማምጣት፤ የታፈኑ የዴሞክራሲ መብቶችን ለማምጣት ይኼን ማድረግ ግድ ነው፡፡ ለህዝቡም የተሟላ መብቱን ለማጎናፀፍ ህጋዊና ህጋዊ ያልሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚለውን ሰብሮ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስርዓት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል ድርድር መኖር አለበት እየተባለ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች በኩል ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡

ማያ፡- በሀገራችን እየተስተዋለ እንደሚገኘው በዘር መጠቃቃት፤ የንብረት መቃጠልና ሌሎችም ጥፋቶች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ እስክንድር፡- እኔ መጀመሪያ ትፈታለህ ስባል፤ ‹ስፈታ ለሚዲያ ምን እናገራለሁ› የሚል ጥያቄ ነው የመጣብኝ፡፡ ያንንም ለመመለስ ትንሽ ነገር ሞነጫጭሬ ካልሲዬ ውስጥ ደብቄ ነው ያወጣሁት፡፡ እስር ቤት ሆኜ ስሰማ የሚያመኝን ነገር ነው የፃፍኩት፡፡ የብሄር መጠቃቃት፣ የንብረት ቃጠሎዎች፤ ያሳዝኑኛል፡፡ መስዋዕት የከፈልነው ይኼንን ለማጥፋት ነበር፡፡

መስዋዕትነት እየተከፈለ ያለውም ለዚህ አልነበረም፤ ለመጠፋፋት አይደለም፡፡ ከኢህአዴግ የተሻለ ነገር ለማምጣት ነው፡፡ ኢህአዴግን የምንበቀለው የተሻለ ስርዓት በመገንባት ነው፡፡ ናሽናል ፓርቲ የአፓርታይድ መሀንዲስ ነው፡፡ ኤ ኤን ሲ ተቀበለው፡፡ ይኼንን ፓርቲ በመደምሰስ ሳይሆን ለዓለም ሞዴል የሆነ ዴሞክራሲ በመገንባት ነው ያሳየው፡፡ በታሪክ ፊት አዋርዶታል፤ አሸንፎታል፡፡

ናሽናል ፓርቲዎች ነጮቹን ሊጨርሱን ነው ብሎ ነበር፡፡ ‹‹ጥቁሮቹ ነጮቹን ገርፈው ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ሊጨምሩ ነው›› ብለው ነበር፡፡ኤ ኢን ሲ የገነባው ዴሞክራሲ ግን ለናሽናል ፓርቲ ቦታ ነበረው፡፡ እንደውም በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተወዳድሮ ሶስተኛ ነበር መሰለኝ የወጣው፡፡ ከተጠበቀው በላይ የተሻለ ድምፅ አግኝቶ ነበር፡፡ ሁሉንም የዴሞክራሲው ተጠቃሚ ነበር ያደረጋቸው፡፡ በታሪክ ፊት እርቃኑን አስቀርቶታል፡፡ በታሪክ ፊት ተወቃሽ አድርጎታል፡፡

ኢህአዴግ ላይ በቀል የሚፈልግ ካለ ይኼ ነው መንገዱ፡፡ ኢህአዴግን በመደምሰስ አይደለም መበቀል የሚቻለው፤ ከኢህአዴግ የተሻለ ስርዓት በማምጣት ነው፡፡ ኢህአዴግ ላይ የሚመጣ ለውጥ ነው ማምጣት ያለበት፡፡ ዴሞክራሲን በማስፈን ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ይኼ ነው መንገዱ፡፡ የብሄር መበጣበጥ መንገዱ አይደለም፡፡ የጥፋት መንገድ ነው፡፡

ይኼ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት አይደለም፡፡ ከኛ ቁመትና ማንነት ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ አይመጥነንም፡፡ ይኼ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት በኩልም በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች መቆም አለባቸው፡፡ የሀይል እርምጃው መገታት አለበት፡፡

የብሄር መጠቃቃትንና የፋብሪካ ማቃጠሎችን እንደምናወግዘው፤ በዛው ትንፋሽ ደግሞ መንግስትም በህዝብ ላይ መተኮስ የለበትም፡፡ የኛ አብዛኛውን ሰላማዊ ሰልፍ ሰላማዊ ነው፡፡ ወደ ብጥብጥ የሚሄደው ሲተኮስበት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ይኼኛውም ኃላፊነት አለበት፡፡ በህዝብ ላይ መተኮስ የሞራል ወንጀልም ነው፤ በህግም ያስጠይቃል፡፡

ማያ፡- መንግስት ያሉትን ችግሮች ለማረጋጋት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ደንግጓል፡፡ አዋጁ ለችግሩ መፍትሄ ያመጣል ብለህ ታስባለህ?

አቶ እስክንድር፡- በፍፁም….በምንም ተአምር፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢህአዴግ ውስጥ ሁለት አዝማሚያዎች አሉ፡፡ በኢህአዴግ አመራሮች ውስጥ ለውጥ ፈላጊ አለ (ተራ አባሎቹን አይደለም፡፡ እነርሱ ከህዝብ የተለየ ፍላጎት የላቸውም፤ ግን የድርጅታቸው ባለቤት ስላልሆኑ ድምፅ የላቸውም) በህዝቡ ውስጥ የተከሰተውን የለውጥ ፍላጎት ተመልክቶ መለወጥ አለብን የሚል ሀይል አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ በሃይል መቀጠል እንችላለን፤ ክንዳችንን ማበርታት ነው የሚገባን፤ ስለተለሳለስን ነው ይኼ ሁሉ ረብሻ የመጣው፤ የተደራጀ ህዝብ አይደለም፤ የት ይደርሳል፤ እንኳን ይኼንን አይደለም ደርግን ደምስሰናል ብሎ በእብሪትና በትምክህት የተወጠረ አለ፡፡

በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህግና ደንቡን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የጭቆና ስርዓቱን ለማስቀጠል የመፈለግ ነገር ነው የሚታየው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው ለዚህ ሀይል ፍላጎት ነው፡፡ ለውጡን የሚፈልገው ሀይል ፍላጎት አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየነውን እኛን ትተህ፤ የኢህአዴግ አጋር የሆኑት ምዕራባውያን፣ ለ27 ዓመታት ከጎኑ የቆሙት ለጋሽ ሀገራት አያዋጣም እያሉት ነው፡፡

በፊት በህዝቡ ውስጥ የነበረው የፍርሀት ድባብ አሁን የለም፡፡ በጉልበት አልገዛም እያለ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ስርዓቱ ለቀጣይ ጥቂት ዓመታት ማስቀጠሉ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡

ስለዚህ አንደኛው መንገድ ሁሉን አቀፍ የሆነው የድርድሩ መንገድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደመፍትሄ ይዞ የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ለማዳፈን ነው፡፡ ይኼ ወደጠባቡ እና ጨለማው መንገድ የሚወስደን ነው፡፡ ያለመረጋጋቱ ምንጭ የፀጥታው ችግር አይደለም፤ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው መፍትሄውም ፖለቲካዊ ነው፡፡

ምንጭ:- ማያ ጋዜጣ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here