Home Uncategorized ከተማ ውስጥ ፊደል ለቃሚ ከማሰማራት በመጻፍና ማንበብ ላይ አበክሮ መስራት!

ከተማ ውስጥ ፊደል ለቃሚ ከማሰማራት በመጻፍና ማንበብ ላይ አበክሮ መስራት!

SHARE

ከሰሞኑ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ “የአጻጻፍ ግድፈት አለባቸው” በሚል ሰበብ የበርካታ የንግድ ድርጅቶች ማስታወቂያዎች እየተነቀሉና እየተቀደዱ ሲጣሉ እየተመለከትን ነው።

ይህን ሁኔታ በአንድ በኩል “አግባብ አይደለም” በማለት የሚቃወሙት እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊቱ “ቋንቋውን ከማስፋፋትና ከማስተማር” ጋር በማያያዝ ጥሩ ነው የሚሉ ሀሳቦችን አድምጠናል።

እኔም ይህን ሁኔታ “አግባብ አይደለም” ከሚሉት ወገን ሆኜ ሀሳቤን ማቅረብ ፈለኩ።

ላለፉት 26 አመታት በክልሉ ለትምህርትና ለስራ አገልግሎት የዋለው አፋን ኦሮሞን ለማሳደግና ለማስፋፋት በርካታ መልካም ነገሮች ሲከናወኑ አይተናል። ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመማራቸው ከሚያገኙት ከፍተኛ የእውቀት ፋይዳ በዘለለ አፋን ኦሮሞ በዘመናዊ ጎዳና እንዲጓዝ ለማድረግ ያለው ድርሻ እጅግ ከፍ ያለ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የግብር ይውጣ ውሳኔዎች ሲወሰኑና ህዝቡን መላ ቅጥ ሲያሳጡ ተመልክተናል። በተለይም ቋንቋውን ከፖለቲካ ጋር የሰነቀሩት ወገኖች እርምጃዎቻቸው በሙሉ እልህ፣ ንዴትና ቁጣ በሚስተዋልበት መልኩ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ማመልከቻ ቀዶ ከመጣል ጀምሮ ከሌላ ቋንቋ ጋር የተቀየጠ አፋን ኦሮሞ የሚናገር ሰው ሲሰሙ ጸብ ጸብ የሚላቸውንም እንዲሁ በአይን አይተን በጆሮ ሰምተን እናውቃለን።
ይህ በቋንቋ ማህበራዊነትና በቋንቋ የእድገት ሂደት ውስጥ ጥቂት ሀሳብ ላለው ሰው ድርጊቶቹ ሰዋዊ ካለመሆናቸውም በላይ ለቋንቋው እድገት ከሚሰጡት ጠቀሜታ ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን በደንብ ይገነዘባል።

ቋንቋው እንዲያድግ እንደ ማንኛውም ቋንቋ መሰረታዊውን መንገድ መከተል ይኖርበታል። ቋንቋ ህጻናት በሚያድጉበት አካባቢ የሚነገር ከሆነ፣ ህጻናት በትምህርት ቤት አስፈላጊውን ግብአት ተሟልቶላቸው የሚማሩት ከሆነና ቋንቋው የሚወደድ እና በፍላጎት እንዲማሩት በተለያዩ የጥበብ ውጤቶች (ስእል፣ ሙዚቃ፣ ድራማ…ወዘተ) ተሰናስሎ የሚቀርብ ከሆነ ወደድንም ጠላንም የቋንቋውን እድገት ማንም ሊገድበው አይችልም።
በተለይም ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለምርምርና ለጥናት ውሎ መጽሀፍቶች እየታተሙ ለህብረተሰቡ በገፍና በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርቡ ከሆነ ቋንቋው የተሸከመውን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች እንኳን ለእለት ኑሯቸው የሚጠቀሙበት ህዝቦች ይቅርና በሌሎችም ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑ አይቀሬ ነው።

ይሁን እንጂ ፖለቲከኞች እንዲህ ያለውን መሰረታዊ ነገር መተግበር ተስኗቸው የቋንቋው አጻጻፍ በደንብ ሳይገባው ከትምህርት ቤት በወጣ ማስታወቂያ ጸሀፊ የተጻፉ ማስታወቂያዎች በመንቀልና በመቅደድ በየከተማው ፊደል የሚለቅም ቡድን ማሰማራታቸው “እውን ለቋንቋው እድገት ስለተጨነቁ ነውን?” የሚል ጥያቄ ያጭራል።

በጣም ተራ የሆነ ጥያቄ ብናነሳ እንኳ “ማን ነው እነዚያን የስህተት ማስታወቂያዎች የጻፋቸው? ለምን በስህተት ተጻፉ? ሆን ብለው ነው ወይስ ከእውቀት ማነስ?…” እያልን ችግሩ የት እንዳለ ማወቅ እንችላለን። ከዚያ አለፍ ስንል ደግሞ የንግድ ማስታወቂያዎችን በአንድ ሳምንት ቀዳዶና ነቃቅሎ በመጣል ሊፈጠር የሚችለውን የንግድ ኪሳራ ድርጊቱን ፈጻሚው ይረዳዋል? እውን በአንድ ሰሞን ዘመቻ የፊደል ግድፈቶችን ማረቅ ይቻላል?

እውነት ለመናገር ድርጊቱ ቀኝና ግራ የሌለው የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ማንም አይስተውም። ይሁንና ግን የቋንቋ ስህተት የሚታረመው በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ብቻ ነው። ማስተማር! ማስተማር! ማስተማር!!….በአንድ ሰሞን ዘመቻ የፊደልም ሆነ የቋንቋ ግድፈት ሊታረም አይችልም። ~ ባይ ነኝ!

(የትነበርክ ታደለ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here