Home Uncategorized የቂሊንጦ ቃጠሎ ሚስጥሮች በጨረፍታ

የቂሊንጦ ቃጠሎ ሚስጥሮች በጨረፍታ

SHARE

~”የሰው እጅ ጣት ተቆርጦ ቆሻሻ ጋር ተጠርጎ ተጥሏል። ይህን ከቃጠሎው በኋላ ቤት ያፀዱ እስረኞች ነግረውናል። የሰው ልጅ እጅ እና እግር ከቆሻሻ ጋር ተቀብሯል። የምንጠይቀው ወይ እኛ ገድለናል በሉ ወይም ለቤተሰብ ይሰጥ ነው። ቴዎድሮስ የሚባል ልጅ ተገድሎ የት እንደተጣለ አይታወቅም። መታወቅ ስላለበት ነው።” 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ

(በጌታቸው ሺፈራው)

የቂሊንጦ እስር ቤት ደህንነት እና ጥበቃ ኃላፊ ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ በቃጠሎው ሰበብ በተከሰሱት እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ (38 ተከሳሾች) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ቀርበዋል። ተከሳሾች ዋና ኦፊሰሩ በቃጠሎው ወቅት ሰው እንደገደሉ፣ ሸዋሮቢት ወስደው እንዳሰቃዩዋቸው፣ ለቃጠሎው ኃላፊዎቹ ተጠያቂ እንደሆኑ፣ እነ ገ/ማርያም በቃጠሎው ወቅት የትግራይ ተወላጆች እየነጠሉ ከግቢ እንዳስወጡ፣ ተገድለው አስከሬናቸው ለቤተሰብ ሳይደርስ የቀሩ እስረኞች እንዳሉ በመስቀለኛ ጥያቄዎቻቸው አመልክተዋል። ተከሳሾቹ ካቀረቡት መካከል፣ የ31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ መስቀለኛ ጥያቄና የዋና ኦፊሰሩ መልስ ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ይመስላል!

ጌታቸር እሸቴ:_ የምንመሰክረው በአሰሩብን ሰዎች ላይ ነው። ትናንት ምስክሩ ሲመሰክሩ እስረኛ ሊያመልጥ ሲል መጀመርያ እግሩን፣ ደረጃ በደረጃ፣ ከዛም ራስ መትተው እንደሚገድሉ ተናግረዋል። በአሰሩን ሰዎች ስለሆነ እየመሰከርን ያለነው ለደህንነታችን ያሰጋናል። ጥበቃ ያሰፈልገናል።

ጌታቸር:_ ታራሚ በበዓል ወቅት ገንዘብ ይሰበስባል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይሰበስብም

ጌታቸር:_ይሰበስባል አይሰበስብም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላውቅም

ጌታቸር:_ ከእናንተ ጋር አብረው የሚሰሩ የእስረኛ ኮሚቴዎች አሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ እንደ አንተ ያሉ!

ጌታቸር:_ እኔ የክልል አስተዳደር እንደነበርኩ ያውቃሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አውቃለሁ

ጌታቸር:_ በሽብር የተከሰሱ እስረኞች ላይ እኛ የቤት አስተዳደሮች በምንሰጠው መረጃ መሰረት ልዩ ፍተሻና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ይፈተሻል፣ ክትትል ይደረጋል።

ጌታቸር :_ በሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ግቢ ውስጥ ሱቅ፣ ካፌ……ጥቅማጥቅም የሚያስገኙ ነገሮች ላይ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም አይደል?

ዐቃቤ ሕግ:_ የክሱ አካል አይደለም። በዋና ጥያቄም አልተጠየቀም። ተከሳሽ ከራሱ አግባብ ነው መጠየቅ ያለበት ስለ ሌሎች ተከሳሾች ሊጠይቅ አይገባም።

ጌታቸር እሸቴ:_ የጠየኩት ስለ ሌሎች ተከሳሾች አይደለም። ከአሁን ቀደም የተመሰከረበት ጉዳይ ነው። ጥያቄዬን እንድቀጥል ይፈቀደልኝ!

ፍርድቤቱ:_ ጥያቄው አግባብ ነው ይቀጥል!

ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሹ የሚሉት በሽብር የተከሰሱት በልዩ ልዪ የስራ መደብ አትመድቡም፣ አድሎ ታደርጉባቸዋላችሁ ነው!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይገባም የሚባል የለም!

ጌታቸር እሼቴ:_ እኔ በሽብር ተከስሼ ነው የገባሁት?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በምን እንደገቡ አላስታውስም።

ጌታቸር እሼቴ:_ ነሃሴ 28/2008 ዓም የየቤቱ አስተዳደሮች አስተዳደር ቢሮ መመሪያ ተሰጥቶን ለታራሚ ትዕዛዝ እንድንሰጥ ልከውናል!

ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም:_ አላኩም

………
ጌታቸር እሸቴ:_ ረብሻው የተነሳው በምግብ ጥያቄ ነው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሼቴ:_ ዞን 2 ወልደሚካኤል ኃለፎምን ያውቁታል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አውቀዋለሁ

ጌታቸር እሸቴ:_ ሰጠኝ ሙሉ፣ ወጋየሁ ረጋሳ፣ መድሃኒት፣ አብዲሳ ቦካ፣…… ያውቋቸዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላውቃቸውም

ጌታቸር እሼቴ:_ አባይ ነህ የ2ኛ ቤት አስተዳደር፣ ያኬት የ4ኛ ቤት አስተዳደር፣ ወጋየሁ ኦሮሞነው፣ መድሃኒት አማራ ነው። ኮሚቴ ናቸው። የእናንተ ረዳት ናቸው። ወልደሚካኤል ግን ምንም ስራ ሳይኖረው፣ ሳያግዛችሁ ያስታውሱታል?

ዐቃቤ ሕግ:_ ጥያቄው መጠየቅ የለበትም ብሎ መቃወሚያ አንስቷል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ጥያቄውን አልፌዋለሁ!

ጌታቸር እሸቴ:_ እርስዎ የቃጠሎው ሰዓት ዞን 2 በመስጊዱ በኩል ቆርቆሩ አጥሩን ገንጥለዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር: _ አልገነጠልኩም

ጌታቸር እሼቴ:_ ሜዳ ላይ አንድ ረዥም ቀላ ያለ ፖሊስ ወደላይ ጥይት ሲተኩስ በጥፊ መትተው መሳርያውን አልቀሙትም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም: _ አልቀማሁትም

ጌታቸር እሸቴ:_ አብዲሳ ቦንካ የወለጋ ልጅ ነው፣ ሰጠኝ ሙሉ የጎንደር ልጅ ነው በጥይት አልመቷቸውም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልመታሁም

ጌታቸር እሸቴ: _በወቅቱ ሽጉጥ ይዘው ነበር?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልተኮስኩም

ጌታቸር እሼቴ:_ እኛ አድኑን እያልን በቀኝ እጅዎት ሽጉጥ፣ በግራ እጅዎት ወልደ ሚካኤል ኃለፎም እና ከፊት ደግሞ ታደለ ብርሃኑን ይዘው ከግቢ አላስወጡም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላስወጣሁም

ጌታቸር እሼቴ:_ ገመቹ የሚባል ፖሊስ ያውቃሉ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ከሚጠየቁት አንዱ ነው

ጌታቸር እሼቴ:_ እርስዎ ወልደሚካኤል ኃለፎምን እና ታደለ ብርሃኑን ይዘው ሲወጡ “ለምን በዘር እየመረጥክ ታስወጣለህ? እኔም ኦሮሞ እየመረጥኩ ላስወጣ ወይ?” ብሎ አልጠየቅዎትም?

ዋና ኦፊሰር:_ አላለም

………

ጌታቸር እሼቴ:_ ሸዋ ሮቢት አብረውን ሄደዋል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ዐቃቤ ሕግ:_ መቃወሚያ አለን። እኛ እያስመሰከርን ያለነው ስለ ነሃሴ 28/2008 ዓም እንጅ ከዛ በኋላ ስላለው አይደለም። በጭብጡም አልተያዘም። ጥያቄው ውድቅ ይደረግልን።

ጌታቸር እሸቴ:_ እኔም እየጠየኩ ያለሁት ስለ ነሃሴ 28 ነው። ጥያቄዬን እንድቀጥል ይፈቀድልኝ!

ፍርድ ቤቱ:_ ጥያቄው መልስ ተሰጥቶበታል። ይቀጥሉ!

ጌታቸር እሼቴ:_ ነሃሴ 28 ማታ 4 ሰዓት አንገትዎት ላይ ሽርጥ አድርገው ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ወስደውናል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስንወጣ ሁሉም ታራሚ ዕቃ ይዞ ነበር?

ዋና ኦፊሰር:_ አላስታውስም

ጌታቸር እሸቴ:_ ትናንት እቃ ሰብስበናል ብለው ስለመሰከሩ ነው!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የአንገት ሀብል፣ የጣት ቀለበት፣ መነፀር፣ ጫማ፣ ልብስ… … እያስወለቃችሁ ከግቢ እንድንወጣ ነው ያደረጋችሁ አይደል?

ዋና ኦፊሰር:_አልወሰድንም

ጌታቸር እሸቴ:_ በባዶ እግር ነው የወሰዳችሁን?

ዋና ኦፊሰር:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የሰበሰባችሁት ንብረት ምን ተደረገ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ተሰብስቧል። ከዛ በኋላ አላውቅም።

ጌታቸር እሸቴ:_ ከሸዋ ሮቢት ስንመለስ፣ ልብሳችንና የዘረፋችሁትን ንብረት ስጡን ስልዎት፣ “የማረሚያ ቤቱን ንብረት እንዳወደማችሁት፣ የእናንተንም ንብረት አውድመነዋል” አላሉኝም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላልኩም

ጌታቸር እሸቴ:_ የታራሚ መነፀር፣ ገንዘብ፣ የጣት ቀለበት…… ንብረት ተወስዷል አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላየሁም

ጌታቸር እሸቴ:_ አላዩም

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አላየሁም

ፍርድ ቤቱ: _የተወሰደ ገንዘብ አለ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ የተወሰደ የለም። አላውቅም።

ፍርድቤቱ:_ እርግጠኛ ከሆኑ የለም ይበሉ!

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተወሰደም

ጌታቸር እሸቴ:_ የተሰበሰበ ንብረት አልነበረም?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ሻንጣና ፔስታል ተሰብስቧል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ታዲያ የት ሄደ?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ ዝናብ መትቶት፣ ገምቶ ተወግዷል።

ጌታቸር እሸቴ:_ ትናንት ጠሃ እና ቴዎድሮስ የሚባሉ መረጃ ይሰጡን ነበር ብለዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ የት ናቸው ተብለው ሲጠየቁም፣ ሞተዋል ብለዋል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ

ጌታቸር እሸቴ:_ ቴዎድሮስ ማለት ጠያቂ የሌለው ገድላችሁ የቀበራችሁት ልጅ ነው አይደል?

ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አይደለም

ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሽ አግባብነት ባለው መንገድ ይጠይቁ!

ጌታቸር እሸቴ:_ አሻሽላለሁ። ግን እርስዎ (ግራ ዳኛው) ከአሁን ቀደም በነበረው ሂደቶች ስላልነበሩ ይሆናል። ስንናገር ቆይተናል። የሰው እጅ ጣት ተቆርጦ ቆሻሻ ጋር ተጠርጎ ተጥሏል። ይህን ከቃጠሎው በኋላ ቤት ያፀዱ እስረኞች ነግረውናል። የሰው ልጅ እጅ እና እግር ከቆሻሻ ጋር ተቀብሯል። የምንጠይቀው ወይ እኛ ገድለናል በሉ ወይም ለቤተሰብ ይሰጥ ነው። ቴዎድሮስ የሚባል ልጅ ተገድሎ የት እንደተጣለ አይታወቅም። መታወቅ ስላለበት ነው። በፍርድ ቤቱ ጫና እየተደረገብኝ ነው። ካልሆነ አቁም በሉኝ ጥያቄዬን ላቁም!

ፍርድ ቤቱ:_ ጥያቄው ታልፏል! ሌላ ጥያቄ ካለዎት ይጠይቁ!
………
……

አግባው ሰጠኝ:_ እኛ ክስ ላይ ሞቷል ተብሎ ከተጠቀሰው ሰው በላይ ሰው እንደሞተ ለማሳየት ነው። ምስክሩ ራሳቸው የገደሉትን፣ ነገር ግን ክስ ላይ ያልተጠቀሰ ሰው እንደሞተ ስላመኑ ጥያቄያችን እንቀጥል።

(ሌሎች ተከሳሾችም በቂሊንጦ ቃጠሎ ተገድለው ለቤተሰብ አስከሬናቸው ያልተሰጠ፣ ክስ ላይ ስማቸው ያልተጠቀሱ አሉ። ምስክሩ ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም ይህን እያመኑ በመሆኑ ለማጣራት እንዲቻል ጥያቄው ይቀጥል በሚል ጥያቄው እንዲቀጥል ፍላጎታቸውን ገልፀዋል። ፍርድ ቤቱ አልፈቀደም!)

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here