Home Uncategorized ደርግና ህወሀት በማዕከላዊ ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም – በሶስት ምክንያቶች።

ደርግና ህወሀት በማዕከላዊ ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም – በሶስት ምክንያቶች።

SHARE

መሳይ መኮንን 

ብዙ ጊዜ ሃይለማርያም ሲናገር ያዝናናኛል። በሱ ንግግር ከመዝናናት ባለፈ የተናደድኩበት ጊዜ ስለመኖሩ አላስታውስም። ባለፈው ረቡ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይለማሪያም አናደደኝ። ”በደርግ ጊዜ የሰው ልጅ ማሰቃያ የነበረው ማዕከላዊ……” ብሎ ሲጀምር ትኩር ብዬ አየሁት። አይኑ እንኳን አይርገበገብም። እኔ ግን በንዴት ቦግ አልኩኝ። እንዳልኩትም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የትኛውም የህወሀት ዲስኩር፡ በሃይለማርያም አንደበት ሲመጣ ቶምና ጄሪን እንደማየት በፈገግታ አልፈዋለሁ። የረቡ ዕለቱ ግን ከውስጥ ጠቅ የሚያደርግ ንዴት ሰውነቴን ነዘረኝ። ደግሜ ደጋግሜ አየሁት። በደጋገምኩት ቁጥር የማይበርድ ንዴት ይንጠኛል። ለምን ይሆን?

ከማዕከላዊ የሰማናቸው የቶርቸር አሰቃቂ ዜናዎች፡ ስቃዮች፡ የጣር ድምጾች ከጆሮአችን ጓዳ ሳይወጡ ሃይለማርያም ስለደርግ ዘመን ሲያወራ መስማት በእርግጥም ያማል? ከደርግም በከፋ መልኩ በዘር ማንነታቸው እየተዘለፉ፡ ብልታቸው የተኮላሸ፡ ጥፍሮቻቸው በጉጠት የተነቀሉ፡ ጡታቸው በኤሌክትሪክ ሽቦ የተተለተሉ፡ በርበሬ ታጥነው፡ የገማ ጨርቅ በአፋቸው ተወትፎ ወፌላላ ተዘቅዝቀው የተገረፉ፡ በእግራቸው ተራምደው ገብተው በቃሬዛ አስክሬናቸው የወጣ፡ የስንቱን ወጣት ስቃይና መከራ እየሰማን ሀዘን ልባችንን ወግቶት ባለበት በዚህ ወቅት ”ማዕከላዊ በህወሀት ዘመን ኩሪፍቱ ሎጅ ነው” ማለት የቀረውን የሃይለማርያምን ደረቅ ውሸት ከመስማት በላይ ምን ቅጣት አለ? ሃይለማርያም ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ሆኖ ”ማዕከላዊ በደርግ ዘመን….” እያለ ሲያላዝን በአንድ ኪሎሜትር ርቀት አራዳ ፒያሳ ከሚገኘው ማዕከላዊ የኢትዮጳያ ልጆች በህወሀት ገራፊዎች ቶርቸር እየተደረጉ ነበሩ።

ደርግና ህወሀት በማዕከላዊ ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም። በሶስት ምክንያቶች። አንደኛው ከዘመን አንጻር ነው። ሁሌም ዛሬ ከትላንት ይሻላል። ነገ ደግሞ ከዛሬ። የሰብዓዊ መብት፡ ዲሞክራሲ፡ እኩልነት፡ ፍትህና ነጻነት ዓለምን እየዋጁ፡ የበላይነትን ይዘው የሀገራት የዕድገት መለኪያ በሆኑበት ዘመን የተፈጠረው ህወሀት ከትላንቱ ደርግ ጋር በአንድ ሚዛን መቀመጥ አይገባውም። ሁለተኛው ምክንያት ደርግ ማዕከላዊን በማሰቃያነት የተጠቀመው ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነው። የቀይ ሽብር ዘመን ካበቃ በኋላ በማዕከላዊ ቶርቸር የሚፈጸም መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ላገኝ አልቻልኩም። እናም ከ17 ዓመቱ የደርግ የስልጣን ጊዜ ማዕከላዊ በማሰቃያነቱ የዘለቀው ከአምስት አመታት በላይ አይሆንም። ህወሀት እነሆ ለ27ዓመታት ማዕከላዊን የኢትዮጵያውያን የስቃይ ማዕከል አድርጎ በመጠቀም የእድሜውን ያህል ቆይቷል።

ሶስተኛው ምክንያት በደርግ ዘመን ገራፊዎቹ ወይም ገዳዮቹ ከአንድ ብሄር የተወለዱ አይደሉም። ስቃይ የሚደርስባቸው ኢትዮጵያውያንም በዘር ማንነታቸው ተሰፍረው አልነበረም። በህወሀት ጊዜ ገራፊዎቹና ገዳዮቹ ከአንድ ወገን፡ ስቃይና መከራን የሚቀምሱት ደግሞ በዘር ማንነታቸው በህወሀት መዝገብ ”ጠላት” የተደረጉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ነው። ሀብታሙ አያሌው እንደነገረን ”ትግርኛ ቋንቋ በሰማሁ ቁጥር የማዕከላዊ ስቃይ እየተመላለሰ ያስጨንቀኛል።” ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ እንዳጫወትችንም ”መቀሌ እስር ቤት ያለሁ ነው የመሰለኝ።” ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንደሚለውም ”ማዕከላዊ የህወሀት የምርኮ ቦታ እስኪመስል ገራፊ ከትግራይ የተሰባሰቡበት ቦታ’

ለማንኛውም ሃይለማርያም ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ አናዶኛል። ከዚህ በላይ ምንም ቢናገር የሚያናድድኝ አይመስለኝም። በተረፈ ህወሀት ማዕከላዊን የመዝጋት ሞራል የለውም። ህንጻ ቢዘጋ ምን ትርጉም አለው? ከማዕከላዊ የከፉ ስንት ስውር የማሰቃያ ቦታዎች እንዳሉ እናውቃለን። በሀሽሽ በጦዙ፡ በአልኮል በናወዙ፡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በደረቀባቸው ነውረኛ የትግራይ ደህንነቶች በየስውር ማሰቃያ ቤቱ እየተፈጸሙ ያሉትን ግፎች ሂሳብ የምናወራርድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የማዕከላዊ የስቃይ ዘመን የሚያከትመው በህወሀትን መቃብር ላይ ነው።

‘አንዳንዶች’

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፌስ ቡክ ገጽ ላይ ስምንት ጊዜ ተቀያይሯል። ፋና ማልዶ ጠዋት የነገረንን ከቀትር በኋላ ለዋውጦታል። ሲጀምር በይቅርታ ኋላ ላይ በምህረት፡ ጠዋት ”ሁሉም”፡ ምሽት ላይ ”አንዳንዶች”፡ ንጋት ላይ ”የፖለቲካ እስረኞች፡ ረፋድ ላይ ”ፖለቲከኞች”፡ አመሻሽ ላይ ”ጥፋት የሰሩ ግለሰቦች”፡ ….መግለጫው ስንቴ ተደለዘ፡ ስንት ግዜ ተሰረዘ። ጭራሽ በነጋታው ያላልኩት ነው የተጠቀሰው ብሎ ሃይለማርያም ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱን ሰማን። ”አንዳንዶች” በሚል ይታረምልኝ ብሏል– ህወሀት በሃይለማርያም በኩል። ”አንዳንዶች” እነማን ይሆኑ?

ድሮም ቅንነት የጎደለው፡ ከአንጀት ያልዘለቀ፡ በውሸት የተለበጠ፡ ከተመረዘ ጭንቅላት የተጨመቀ፡ ክፋት ከሞላው ልብ የፈለቀ፡ ደም ባጨቀየው እጅ የተጻፈ መግለጫ ነው። እየዋሹ እርቅ የለም። እየቀጠፉ መግባባት አይታሰብም። ዕውነት ከእርቅ ይቀድማል። መግባባት ሀቅን ይፈልጋል። ህወሀት ከዕውነት ጋር የተጣላ፡ በውሸትና ቅጥፈት የተሞላ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድን ጥቁር ዘመን ሲሸኙት በቅድሚያ ዕውነቱን ተነጋግረው ከዚያም ወደ ዕርቅ በማምራት ነው። የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ታሪክ የተቋጨው የዕውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ፡ ዕውነቱ ፍርጥርጥ ተደርጎ ወደ ዕርቅ በመሸጋገር እንደሆነ እናስታውሳለን። ህወሀት ተፈጥሮው ለዚህ አይፈቅድም። መሪዎቹ ጫካ በነበሩ ጊዜ ከሰውነታቸው ውስጥ የሆነ ተቆርጦ የወጣ፡ የጎደላቸው ነገር ያለ ይመስላል። ዕውነት ያማቸዋል። ውሸት ያለመልማቸዋል። ቅንነትን ይጠየፋሉ። ክፋትን ይመርጣሉ።

ሃይለማርያም የጎረሰውን እንዳለ ተኩሷል። ያጠናውን ቃል በቃል አነብንቧል። የህወሀትን ተራ ውሸትና ጅላጅል ዲስኩር ሳያላምጥ ውጦ፡ አንድም ሳያስቀር ተፍቶታል። በሃይማኖተኝነቱ የሚያውቁት የቀድሞ ወዳጆቹ መቼም ያፍሩበታል።አዲስ ነገር አይደለም። ወዶ ገብ፡ ምርኮኛ፡ የቤተመንግስት እስረኛ በመሆኑ ሲጠሩት ‘አቤት’፡ ሲልኩት ‘ወዴት’ ከማለት ውጪ ምርጫ አይኖረውም።መቼም ወደ ሰውነት ተራ አይመለስም። ተመችቶታል። የህወሀት መቀለጃ እንደሆነ ዕድሜውን ጨረሰው። ስለሃይለማርያም እዚህ ላይ ይብቃኝ።

የ18 ቀናቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዝግ ስብሰባ መጠናቀቁን አስመልክቶ ቅዳሜ የወጣው የተንዛዛና የጠነዛ መግለጫ ለተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጥሩ ነዳጅ ነው ማለት ይቻላል። መግለጫውን ተከትሎ ህወሀት ለህዝብ መጥይቅ በትኗል። መግለጫውን እንዴት አገኛችሁት? በእኛ ተስፋ ታደርጋላችሁ ወይ? አይነት መጠይቅ በጥድፊያ ተበትኖ፡ ምላሹ ተሰብስቦ ውጤቱም በራሱ በህውሀት ተገልጿል። በችኮላ ይሁን አልያም በሌላ ምክንያት እውነተኝእ ውጤቱን ተበትኗል። በዚህም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው መጠይቁን የሞላው ሰው ”እናንተ አትለወጡም። በእናንተም ተስፋ የሚያደርግ የለም።” የሚል እቅጩን ነግሮአቸዋል። የሻምቡ ተቃውሞ ሲጨመርበት፡ በየቦታው ህዝቡ ትግሉን ሳያቋርጥ መቀጠሉ ህወሀት በመግለጫ ጋጋታ ህዝብን ማንበርከክ እንደማይቻለው ተረዳ። እናም ”እስረኞችን እፈታለሁ” የሚል ሌላ አጀንዳ ከፈተ።

አዎን! ህወሀት ለጊዜው አጀንዳ ወርውሮልናል። እነማን ይፈቱ ይሆን? የሚል አርእስት ተከፍቶልን እየተጨነቅን እየተጠበብን ነው። ይህ መሆኑ ለህውሀት ጊዜያዊ እፎይታን ይሰጠዋል። የውጭ መንግስታት፡ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች የህወሀትን ተለዋዋጭና ዋስትና የሌለው መግለጫን ይዘው እያራገቡ መሆናቸውን ታዝቤአለሁ። ለኢትዮጵያ ለውጥ የመጣ፡ አንዳች ታሪክ የተፈጠረ ይመስል ሰሞኑን የወሬ ማጥፋጫ እኛኑ አድርገውናል። ጠዋትና ማታ የሚቀያየረውን የህውሀትን አቋም ወደጎን ተትቶ ”ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ ልትፈታ ነው። ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው።” የሚለው ወሬ በውጪው ሚዲያ በርክቷል።

በእኛው መንደርም ያለፉትን ሁለት ቀናት የታየው ስሜት ለትዝብት የሚዳርገን ነው። ያለልክ የፈነጠዙ፡ ደስታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው በእምባ የተራጩ፡ አንዳንዶች እንደውም ሻንጣቸውን አሰናድተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ለመግባት የወሰኑ መኖራቸውን ሰምተናል። ህወሀት የመጀመሪያ ቃሉ አክብሮ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ቢፈታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሚፈታ አይደለም። በተደጋጋሚ እንደሚባለውም የታስሩለት ዓላማ ሳይፈታ የታሰሩት መፈታታቸው ትርጉም የለውም። ጀግኖቻችን ከተፈቱ መፈታታቸው ሊስደስተን ይገባል። ከዚያ ባለፈ ደስታ አስክሮ አጥወልውሎ እስኪጥለን ሊደርስ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።

በእርግጥ ህወህት የፖለቲካ እስረኞችን ይፈታልን? ሪፖርተር ጋዜጣ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ጠብቁ ብሎናል። እነማን እንደሚፈቱ ግን አልገለጸም። በዋዜማ ሬዲዮ በኩል የወጣው መረጃ ደግሞ ደህንነት መስሪያ ቤቱና ፍትህ ሚኒስቴር በሚፈቱት ሰዎች ላይ መግባባት አልቻሉም። ደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰማይ ዝቅ፡ መሬት ከፍ ቢል የማይፈቱ ብሎ በመዝገቡ የያዛቸው አሉ። ሃይለማርያም የመጀመሪያውን መግለጫ በማግስቱ እንዲቀይርና ”አንዳንዶች” በሚል እንዲስተካከል የተደረገው በደህንነት መስሪያ ቤቱ ትዕዛዝ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ህወሀት አስራአንደኛው ሰዓት ላይም ትዕቢትና ድንቁርና አይለቀውም።

በዚህም ተባለ በዚያ ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እይተካሄደ ነው። ”አንዳንዶችም” ይፈቱ ”ሁሉም” አሁንም ትግሉ ይቀጥላል። ህወሀት የተሳሳተው እየተካሄደ ያለው ትግል በመግለጫ ጋጋታ፡ በአስቸኳይ አዋጅ፡ እስረኞች በመፍታት የሚቆም አድርጎ ማስላቱ ነው ።በእርግጥ የፖለቲካ ስጋውን እየጨረሰ፡ አጥንቱን እየበላ በቁሙ እየሞተ ያለ ስርዓት ሌላ ምርጫ የለውም።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here